ቀጥታ፡

ባለፉት 5 ዓመታት ዓመታዊ የቡና ምርት መጠንን ከነበረበት 500 ሺህ ቶን በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት 5 ዓመታት ዓመታዊ የቡና ምርት መጠንን ከነበረበት 500 ሺህ ቶን በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከቀደሙት ዓመታት  ከፍተኛ ብልጫ ያለው ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል።

ሀገራዊ የቡና ኤግዚቢሽንና የእውቅና መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ቡና ምርትና ወጪ ንግድ አፈጻጸም የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አርሶአደሮች፣ ላኪዎች፣ ማኅበራትና ክልሎች የእውቅና ሽልማት አበርክተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባለፉት 5 ዓመታት ለቡና ምርትና ጥራት መጨመር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። 

በተለይ የቡና ችግኝ ተከላና ጉንደላ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን አንስተዋል። 

በዚህም የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቡና ምርትን ከ 5 ዓመታት በፊት ከነበረነት 500 ሺህ ቶን ወደ አንድ ሚሊዮን ቶን ማሳደግ መቻሉንም ነው ያብራሩት። 

ከገቢ አንጻርም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ ከ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር  በላይ ገቢ ማግኘቷን አንስተው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ይህን አሃዝ ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን የዓለም ከፍተኛ ቡና አምራች ሀገራት አንዷ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። 


 

ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ከመንግሥት በተጨማሪ ላኪዎች የቡና ምርት ጥራትን ለሚያሻሽሉ ተግባራት ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

ላኪዎች ቡና ምርት ላይ ውበት ባለው አስተሻሸግ ዘዴ እሴት ጨምሮ ለወጪ ገበያ ማቅረብ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም አንስተዋል። 

በሌላ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ በዓለም ገበያ ይበልጥ እንድትሳተፍ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል። 

ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከቀደሙት ዓመታት  ከፍተኛ ብልጫ ያለው ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል። 

በቀጣይም የሚገጥሙን ፈተናዎች ሳያቆሙን በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ እንሰራለን ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም