ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በባህል እና በሃይማኖት ያላቸውን እሴቶች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መጠቀም ይገባል

አዲስ አበባ ፤መስከረም 30/2017(ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በባህል እና በሃይማኖት ያላቸውን እሴቶች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መጠቀም እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት በሞሮኮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን ከሞሮኮ የኢንዶውመንትና የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር አሕመድ ተውፊቅ ጋር ተወያይቷል።

የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የሞሮኮ ሕዝብ በባህል እና በሃይማኖት ያሉት እሴቶች ከኢትዮጵያ ጋር መመሳሰል እንዳለው ገልጸው፥ እሴቶቹን በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሞሮኮ የኢንዶውመንትና የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር አሕመድ ተውፊቅ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የነቢዩ መሐመድ ባልደረቦችና ቤተሰቦችን በፈታኝ ወቅት በማስተናገድ የዋለችው ውለታ በሙስሊሙ ዓለም ታሪክ በደማቁ የተጻፈ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በመላው ሙስሊሙ ልብ ውስጥ ያለች ሀገር ናት ብለዋል።

በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል፣ የታሪክና የሃይማኖት ግንኙነት ለማጠናከር ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን የሁለቱ ሀገራትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ለማከናወን በሞሮኮ ይፋዊ ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝ ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም