ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ የ10 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 30/2017(ኢዜአ) ፡-ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ የ10 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ኮይካ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዲዩግ ቾ ናቸው።

የጥራት አመራር አቅም ማጎልበቻ ፕሮጀክት ስምምነት የግብርና እና የተቀነባበሩ የግብርና ምርት ውጤቶች ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ዋንኛ ትኩረቱ እንደሆነ ተገልጿል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) የፕሮጀክት ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ጠንካራ ትብብር የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያን የጥራት መሰረተ ልማት እንደሚያጠናክር እና የግብርናውን ዘርፍና የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።

የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ኮይካ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዲዩግ ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በኮሪያ ጦርነት ወቅት ከ6000 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኮሪያ ሕዝብ ተዋግተው የደም ዋጋ መክፈላቸውን አስታውሰዋል።

የፕሮጀክት ስምምነቱ የኮሪያ ሪፐብሊክ እና የኢትዮጵያ ወዳጅነትን የሚያጠናክር እንዲሁም በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለማምጣትና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ ኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም