ኢትዮጵያ እና ኬንያ በዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ኬንያ በዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ ፤መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ እና ኬንያ በዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ የጀመሩትን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሮስሊን ንጆጉ የተመራ የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል።
ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር እና የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባላትን ያካተተ ነው።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው፥ ኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ስራዎችን ለማጎልበት ያለፈችባቸውን ሕጋዊ፣ተቋማዊና መዋቅራዊ ሂደቶችን እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ለቡድኑ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ለዳያስፖራው ባቀረበቻቸው ተከታታይ ሀገራዊ ጥሪዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ራሱን የቻለ ተቋም እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር መስራት መቻሏ እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ ተግባር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ በርካታ ዳያስፖራ ያላቸው ጎረቤት ሀገራት መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
ሀገራቱ የዳያስፖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የትብብር ተግባራት አጠናክረው መቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።