የዘር እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል የምርምር ስራ ጉልህ ሚና ይጫወታል- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዘር እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል የምርምር ስራ ጉልህ ሚና ይጫወታል- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤መስከረም 30/2017(ኢዜአ)፡-የዘር እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል የምርምር ስራ ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
በማሽላ የዘር ስርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጀታ እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ አመራሮች እና ሳይንቲስቶች ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ የዘር እሴት ሰንሰለት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው የምርምር ስራ ለዘርፉ ያለው አበርክቶ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዘር ለግብርና ዘርፍ ያለውን አስፈላጊነት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የውይይቱ ዓላማ በማሽላ የዘር ስርዓት ላይ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጀታ ጋቢሳ ኤጀታ የማዳቀል ዘር ስርዓት በአሜሪካ ከተጀመረ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን አንስተው በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋር የተናበበ የሰው ኃይልም አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በማሽላ የዘር ስርዓት ላይ የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።