ቀጥታ፡

የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ከተሞች ይገነባሉ - የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 30/2017(ኢዜአ) ፡- የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ከተሞች ለመገንባት እየተሰራ እንደሚገኝ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የአወጋገድ ስርዓቱ መዘመን ከብክለት እና አወጋገድ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚያስችልም ገልጿል።

በአዳማ ከተማ ደንበል የጋራ መኖሪያ ቤቶች 650 የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በተፈጥሯዊ መንገድ የፈሳሽ ቆሻሻን የሚያጣራ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

በምርቃቱ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) ፣ለጋሾች፣ አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ፕሮጀክቱን ቢቢቢሲ በተሰኘ ድርጅት እና በወተርኔት ፕሮጀክት ድጋፍ አማካኝነት መገንባቱንና የአምስት ወራት ጊዜ መውሰዱ ተገልጿል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) በተፈጥሯዊ መንገድ የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት ብለዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አካባቢን በመፍጠር የአካባቢ ብክለትን የመቀነስ፣ የውሃ ጥራትን የማሻሻል እና በተፈጥሯዊ መንገድ ምንም አይነት ኬሚካል ሳይጠቀሙ አትክልቶችን ለማልማት እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ከቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እና ውሃ ብክለት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ማሻሻል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የአወጋገድ ስርዓትን ለማሻሻል የቅንጅት አሰራርን ማጠናከር እና የባለድርሻ አካላትን የጋራ ጥረትን እንደሚጠይቅ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኑረዲን መሐመድ ማጣሪያው በተፈጥሯዊ መንገድና በኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚሰራ ገልጸው በቀጣይ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በሌሎች ከተሞች እንደሚገነቡ ጠቅመዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች በቀጣይም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም