ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማ እንዲሆን በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያ እየተገበረች የሚገኘው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማ እንዲሆን በትብብር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

ከመስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በለንደን ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን ከዩናይትድ ኪንግደም የውጭ፣ ኮመንዌልዝ(የጋራ ብልጽግና ሀገራት) እና ልማት ጽህፈት ቤት(FCDO) ረዳት ዋና ፀሐፊ ኒክ ዳየር ጋር ተወያይተዋል።

ዶክተር እዮብ ተካልኝ ለረዳት ዋና ፀሐፊው የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለውጥ፣ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

መንግስት በኢንቨስትመንት መስክ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መፍትሔ እንዲያገኙ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዩናይትድ ኪንግደም በሀግር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድርድሩ ወቅት ላደረገችው ወሳኝ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ፣ ኮመንዌልዝ(የጋራ ብልጽግና ሀገራት) እና ልማት ጽህፈት ቤት(FCDO) ረዳት ዋና ፀሐፊ ኒክ ዳየር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን ራዕይ በመያዝ እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊ የሆኑትን ማሻሻያዎችን ለመውሰድ ያሳየውን ቁርጠኛ አቋም ማሳየቱንም ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በማሻሻያዎቹ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን ያነሱ ሲሆን የሪፎርም ስራው ውጤታማ እንዲሆን በትብብር እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የዩናይትድ ኪንግደም የፋይናንስ ተቋም ከሆነው የብሪቲሽ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ የጀመረቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና ተቋሙ በኢትዮጵያ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ብሪቲሽ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት እየተደረጉ ያሉ ቁልፍ ማሻሻያዎችን ያደነቀ ሲሆን ለማሻሻያዎቹ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየቱም ተመላክቷል።

በውይይቶቹ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ዋና ዳይሬክተር ሀና ተክሉ መሳተፋቸውን በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም