አዋጊና ተዋጊ ብቻ ሳይሆን አምራች መሆናችንን በተግባር እያሳየን ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦አዋጊና ተዋጊ ብቻ ሳይሆን አምራች መሆናችንን በተግባር እያሳየን ነው ሲሉ የጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ ተናገሩ።

አንጋፋው የጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በ1972 ዓ.ም ታጠቅ ቁጥር ሁለት በሚል ስያሜ ነበር የተመሰረተው።

የጊቤ ወንዝ ሸለቆን ተንተርሶ የተመሰረተው ይህ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ዛሬ ላይ የጦላይ የባለሌላ ማዕረግተኞች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ይሰኛል።

በደርግ ዘመነ መንግሥት ጦላይ ስፓርታ ይሰኙ የነበሩ ወታደሮችን አፍርቷል።

የምልምልም፣ የተዋጊና የአዋጊ ጦር መኮንኖችንም አሰልጥኗል።

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በተሃድሶ ማዕከልነትና በካድሬ ማሰልጠኛነት አገልግሏል።

በጥቅሉ ጦላይ ሁለገብ አገልግሎት ሰጭ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ነው።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህም አያሌ የመሰረታዊ ውትድርና ሰልጣኞችን አስመርቋል።

ጦላይ ከተመሰረተበት ዘመን አንስቶ በግቢው የለማው ደን ልዩ ገፃታ አላብሶታል።

የትምህርት ቤቱ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ እንደሚሉት የባለሌላ ማዕረግ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ጦላይ መልክዓ ምድራዊ ገፅታው ለውትድርና ሥልጠና የተመቸ ነው።


 

በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ዛፎች የተሸፈነ መሆኑም ማሰልጠኛ ካምፑን ልዩ ያደርገዋል።

ጦላይ በዕፅዋትና በዱር እንስሳት ብዝሐ ሕይወቱ ጥብቅ ፓርክ መሰል ልዩ ገፅታ ተላብሷል።

ሌላው የጦላይ ተምሳሌታዊ ተሞክሮ ያለውን ዕምቅ ፀጋ ወደ ልማት በመለወጥ በኩልም ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ሰልጣኝ ሰራዊቱ ከሥልጠና ባሻገር በቆይታው አምራች ሚና እንዲኖረው በግብርናው ልማትና በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰማራ በማድረግ ውጤታማ ሥራ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።

የጦላይ መልክዓ ምድር ለወታደራዊ ሥልጠና ብቻ ሳይሆን የሰጡትን የሚያበቅል ለም መሬት የተቸረ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የሀገሪቱን በምግብ ራስን የመቻል አቅጣጫ በመከተል መሬት ፆም ማደር የለበትም በሚል መንፈስ ምርታማ ተቋም ለመሆን በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በእርሻ፣ በጓሮ አትክልት፣ በእንስሳት እርባታ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ይጠቀሳሉ።


 

በመከላከያ ደረጃ በልማት ሥራዎች የዋንጫ ሽልማት ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው ጦላይ የባለሌላ ማዕረግተኞች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት።

ተጋግዞ ሀገርን ማበልፀግ እንደሚቻል የገለጹት አዛዡ፤በዚህ ዓመት ብቻ 85 ሄክታር መሬት በበቆሎ መልማቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት የሚጠበቅ ሲሆን ምርቱ ለምልምል ሰራዊቱ ምግብነትና ለገበያ እንደሚውል ነው የገለፁት።

ከቦቆሎ በተጨማሪ በመስኖ የሚለሙ ሽንኩርት፣ ሽምብራ፣ ስንዴና የተለያዩ ሰብሎችን እያለማ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከአረንጓዴ አሻራ ጋር በማያያዝ ቡና፣ ሙዝና የተለያዩ ለምግብነት የሚውሉ ቋሚ ሰብሎችን እያለማ ይገኛል።

በሌላ በኩል ሀገራዊና ህዝባዊ አስተሳሰብ በመያዝ የቦረና ሀገር በቀል የከብት ዝርያዎችን በማርባት ውጤት እየተገኘ ስለመሆኑ አንስተዋል።

አዊጊና ተዋጊ ብቻ ሳይሆን አምራች መሆናችንን በተግባር እያሳየን ነው ብለዋል።


 

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ፀጋዎች፣ዕውቀትና የሰው ኃይል በመጠቀም ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በአጠቃላይ በግቢው በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የእንስሳት ተዋፅዖ እያገኘ ነው።

በማኅበራዊ አገልግሎትም የትምህርት ተቋማት ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ አገልግሎቶች በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።

በትምህርት ቤቱ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ሻለቃ አያሌው ባልቻ ትምህርት ቤቱ በብረታ ብረትና እንጨት ሥራዎች ለምልምል ሰራዊቱ የሚያስፈልጉ የመገልገያ መሳሪያዎችን በማምረት ፍላጎቱን ማሟላት የሚያስችል ሥራ ጀምሯል።

ለዚህ ደግሞ ግቢው በተፈጥሮ ኃብት የተቸረ በመሆኑ ከማሽን በስተቀር ሌላ ግብዓት ከውጭ እንደማይፈልግ ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም