ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሞሮኮ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ትሰራለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከሞሮኮ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደምትሰራ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በሞሮኮ ጉብኝት ላይ ይገኛል።

ልዑካን ቡድኑ የመንግሥት የሰላምና ፀጥታ አመራሮች እንዲሁም የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ኃላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶችን ያካተተ ነው።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ጉብኝቱ በኢትዮጵያ እና ሞሮኮ መካከል ያለውን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጎለብት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሞሮኮ የተለያዩ ሃይማኖቶችና ሕዝቦችን ተከባብረው እንዲኖሩ በማድረግ በአፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ ከገነባችበት መንገድ ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግ አመልክተዋል።

የልዑካን ቡድኑ በሞሮኮ ራባት እና ካዛብላንካን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማትን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቡድኑ ከከተሞቹ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም