የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን ልኬት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አዲስ ዘመናዊ መሳሪያ ሥራ ላይ ሊውል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን ልኬት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አዲስ ዘመናዊ መሳሪያ ሥራ ላይ ሊውል ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን ልኬት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አዲስ ዘመናዊ መሳሪያ ሥራ ላይ ሊውል መሆኑን የኢትዮጵያ ሥነ- ልክ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ጨረራ ወይም ራዲየሽን (Radiation) የሚለው ቃል በቀላሉ ሲገለፅ አቅም ወይም ኢነርጂ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሞገድ ወይም በቅንጣት መልክ ሲጓጓዝ ማለት ነው።
የጨረራ ዓይነቶች በዋነኝነት አዮን ፈጣሪ ጨረራ እና አዮን የማይፈጥር ጨረራ በመባል ይጠቀሳሉ።
በጨረራ ምንጭነት ከሚጠቀሱት መካከልም የፀሐይ ጨረራ፣ ለማብሰያነት የሚያገለግሉ የማይክሮ ዌቭ ቁሳቁሶች፣ የሕክምና መሳሪያዎች፣ የሬዲዮ ሥርጭትና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
በእነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች የሰው ልጆች በየዕለት እንቅስቃሴያቸው ለጨረራ የሚጋለጡበት አጋጣሚ የበዛ መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
የዓለም አገራት የጨረራ አመንጪ ቁሶችን ለሕክምና፣ ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎችም አገልግሎቶች እየተጠቀሙበት ይገኛል።
ኢትዮጵያም ለሕክምና ጨምሮ ለሌሎችም አገልግሎቶች የጨረራ አገልግሎትን ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት በዓለም አቀፍ የልኬት አሃዶች መሠረት የጨረራ አመንጪ መሳሪዎችን ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ ያከናውናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅረአብ ማርቆስ፤ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች በተለይም ለሕክምና አገልግሎት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም የራጅ፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድና ሌሎችም የሕክምና አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አንስተዋል።
ለመሳሪያዎቹ አገልግሎት ውጤታማነትና ጉዳቶችን ለመከላከል የልኬት ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ በዚሁ መሠረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የጨረራ አመንጪ የሕክምና እና ሌሎች መሳሪያዎችን የልኬት ትክክለኛነት ማረጋገጥ የሚያስችል ማዕከል በአዲስ መልክ በማቋቋም ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም በ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ዘመናዊ የመሳሪያ ግዥ መከናወኑን አስታውሰው፤ በቅርቡ ተከላው ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፓንቲክ ኤክስሬ፣ ሲጂይም ሶርስ እና ሌሎችም የስነ ልክ መሰሪዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።