በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች የከፋ ጉዳት አላደረሱም - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች የከፋ ጉዳት አላደረሱም
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆና አካባቢው የተከሰቱ የሥነ-ምድር አደጋዎች የጎላ ጉዳት ያደረሱበት ዘመን እንደሌለ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መሰንጠቅ፣ የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታ፣ ሱናሚ፣ የመሬት መንሸራተትና ሌሎችም ዓለም የምታስተናግዳቸው የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው።
የመሬት መንቀጥቀጥ በመሬት ውስጥ አለቶች ግጭት ሲፈጥሩ ወይም ሲላቀቁ በሚፈጠረው ክፍተት ከፍተኛ ድምፅ ሲገባ የሚከሰት ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ ነው።
የመሬት መንቀጥቀጥና እሱን ተከትሎ የሚከሰት ንዝረት ደግሞ በተለያዩ ዓለማት ከንብረት ውድመት እስከ ህይወት መቅጠፍ የደረሰ አደጋ አድርሰዋል።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1960 በቺሊ የተከሰተውና በሬክተር ስኬል 9 ነጥብ 5 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በምድር ላይ የከፋውና ከፍተኛው ነው።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢጃራ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ መገኛ እንደመሆኗ በተለያዩ ጊዜያት የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሟታል።
የከፋ ጉዳት ባያደርስም በ1900 ዓ.ም 6 ነጥብ 7፣ በ1909 ዓ.ም 6 ነጥብ 8 እንዲሁም በ1961 ዓ.ም 6 ነጥብ 5 በሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አስታውሰዋል።
የመሬት መንቀጥቀጥን ጨምሮ የሥነ-ምድር አደጋዎች በእርግማን ወይም ቁጣ የሚከሰቱ ሳይሆን መሬት ተፈጥሯዊ ሥራዋን እየሰራች ነው ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ መገኛ በመሆኗ የሥነ-ምድር አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ገልጸው፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የሥነ-ምድር አደጋ መቼ ሊከሰት እንደሚችል ማወቅ ባይቻልም፤ እንደ ተቋም የተደራጀ መረጃ መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት የጂኦፊዚክስ ምርምር ሥራ አስፈጻሚ ገነት አሰፋ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ በአለቶች ግጭትና መላቀቅ፣ በእሳተ-ገሞራ፣ በኬሚካልና ኒውክሌር ፍንዳታ እንዲሁም በሰው ሰራሽ መንገድ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች በእሳተ-ገሞራና በአለቶች ግጭት የሚፈጠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በ10 ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ በ4 ነጥብ 9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ በመሆኑ የጉዳት መጠኑ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ፈንታሌ ላይ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ አሰበ ተፈሪና ሌሎችም አካባቢዎች ንዝረት እንደነበር ገልፀዋል።
በኢንስቲትዩቱ የጂኦፊዚክስ ከፍተኛ ተመራማሪ ዕዝራ ታደሰ፤ ሕብረተሰቡ የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ ንዝረት ሲያጋጥም ቅድሚያ በመረጋጋት ለአደጋ ከሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች መታቀብ አለበት ብለዋል።