ቀጥታ፡

በአፍሪካ የእጅ ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ሶስት የኢትዮጵያ ክለቦች ይሳተፋሉ 

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 29 /2017 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ በሚካሄደው 45ኛው የአፍሪካ ክለቦች የወንዶች እና ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና መቻል፣ መቀሌ 70 እንደርታ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

በላዩን ከተማ የሚካሄደው ሻምፒዮና ነገ ይጀመራል።

በውድድሩ ላይ 16 የወንድ እና 11 የሴት በድምሩ 27 ክለቦች እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በወንዶች በመቻል፣ መቀሌ 70 እንደርታ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ክለቦች ትወከላለች።

መቻል በምድብ አራት ከሞሮኮው ዊዳድ፣ ከሴኔጋሉ አስፋ እና ከቤኒኑ አድጂድጃ ክለቦች ጋር ተደልድሏል።

መቻል የመጀመሪያ ጨዋታውን ነገ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ከቤኒኑ አድጂድጃ ቡድን ጋር ያከናውናል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በምድብ 3 ከግብጹ ዛማሌክ፣ ከሞሮኮው ማዋንትአዳ እና ከካሜሮኑ ፍሬንድሺፕ ክለቦች ጋር ተደልድሏል።

ቂርቆስ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን ነገ ከግብጹ ዛማሌክ ቀኑ 8 ሰዓት ላይ ይጫወታል።

በሻምፒዮናው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፈው መቀሌ 70 እንደርታ በምድብ 1 ከግብጹ አል ሃሊ እንዲሁም የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ክለቦች ከሆኑት ኢቶይሌ እና ሲኤፍጄኤሶ ጋር ተደልድለዋል።

ክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ ከግብጹ አል አህሊ ጋር ያደርጋል።

45ኛው የአፍሪካ ክለቦች የወንዶች እና ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

እ.አ.አ በ2023 በኮንጎ ሪፐብሊክ ብራዛቪል በተካሄደው 44ኛው የአፍሪካ ክለቦች የወንዶች እና ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና በወንዶች የግብጹ አል አህሊ በሴቶች የአንጎላው ፕሪሚየሮ ዲ አጎስቶ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም