ኢትዮጵያ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታዋን ከደቡብ ሱዳን ጋር ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታዋን ከደቡብ ሱዳን ጋር ታደርጋለች
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 29 /2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያደርጋል።
የማጣሪያ ውድድሩ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
በምድብ 2 የምትገኘው ኢትዮጵያ ሁለተኛ ጨዋታውን ከደቡብ ሱዳን ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ታከናውናለች።
በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው በዩጋንዳ 3 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል።
ተጋጣሚው ደቡብ ሱዳን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በብሩንዲ 1 ለ 0 ተሸንፋለች።
በዚሁ ምድብ ዩጋንዳ ከብሩንዲ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በኪኖንዶኒ ሙኒሲፓል ካውንስል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በተያያዘም ትናንት በምድብ 1 በተደረጉ ሁለተኛ ጨዋታዎች ታንዛንያ ጅቡቲን 7 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ስታረታ ሱዳን ሩዋንዳን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ውጤቱን ተከትሎ ሱዳን በስድስት ነጥብ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባቷን ያረጋገጠች የመጀመሪያ አገር ሆናለች።
ታንዛንያ እና ኬንያ በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ዘጠኝ አገራት በሁለት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።
የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።