ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ አቢጃን አቀና 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ ጋር ለሚያደርጋቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ኮትዲቭዋር መዲና አቢጃን ማምራቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ጨዋታዎቹ ጥቅምት 2 እና 4 ቀን 2017 ዓ.ም ይደረጋሉ።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ለማጣሪያ ጨዋታው ለ23 ተጫዋቾች መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጥሪ አድርገዋል።

ቡድኑ ከመስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ሲያደርግ ቆይቷል።

ዋልያዎቹ በሞሮኮ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሶስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን ለማድረግ ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ኮትዲቭዋር መዲና አቢጃን ማቅናታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በዚሁ ምድብ የሚገኙት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ታንዛንያ መስከረም 30 እና ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ በምድብ 8 እስከ አሁን ባደረገቻቸው ጨዋታዎች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 0 ስትሸነፍ፣ ከታንዛንያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየቷ የሚታወስ ነው።

ውጤቶቹንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በስድስት ነጥብ ምድቡን እየመራ ይገኛል። ታንዛንያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ጊኒ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛለች።

48 አገራት ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።  

በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም