ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ልማት መረጋገጥ አበክራ ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ልማት መረጋገጥ አበክራ ትሰራለች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ለጋራ ቀጣናዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ባለፈው ሰኞ መካሄዱ ይታወሳል።
በዚሁ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ የሰላም ሁኔታና የኢትዮጵያን ሚና በተመለከተ ኢዜአ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን አነጋግሯል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነቷን በማጠናከር ለጋራ ልማትና እድገት አበክራ እንደምትሰራ ነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ያረጋገጡት።
የቋሚ ኮሚቴው አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በየጊዜው ያላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል።
በተለይም ጎረቤት አገራቱ የሰላም እጦት ሲያጋጥማቸው ቀድሞ ደራሽ በመሆን መፍትሔ በመስጠት እያበረከተች ያለው አስተዋጽዖ ለማንም የሚሸሸግ አይደለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማሳደግና በቀጣናው የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ በጋራ ለመልማት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባልና የኢጋድ ፓርላማ አባል አምባሳደር የሺመብራት መርሻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የበኩሏን አስተዋጽዖ እያደረገች ነው።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በወዳጅነት መንፈስ ለጋራ ልማትና ዕድገት እያደረገች ያለውን ጥረት አገራቱ መደገፍና መተባበር እንደሚገባቸውም ነው የገለጹት።
የምስራቅ አፍሪካ አገራት ድንበር ቢለያቸውም ተመሳሳይ ባህልና እሴት ያላቸው እንደመሆኑ እርስ በርሳቸው መደጋገፍና በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ሌላው የቋሚ ኮሚቴው አባል አምባሳደር ቶፊክ አብዱላሂና አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ይገልጻሉ።
እያደገ ያለን ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል የገቢና ወጪ አማራጭ ወደብ በሰጥቶ መቀበል መርህ ማግኘት ደግሞ የህልውና ጉዳይ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት አገራት በሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ መሠረት በጋራ ተጠቃሚነትና በጋራ ልማት ላይ ያተኮረ ግንኙነት ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።