ትኩረት የሚሻው የአዕምሮ ጤና

የአዕምሮ ጤና አንድ ሰው በዕለት ተለት ኑሮው የሚያጋጥሙ ጫናዎችን ተቋቁሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግና አምራች ዜጋ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው። 

የአዕምሮ ጤና መቃወስ ደግሞ እነዚህን የዕለት ተለት ተግባራት አለማከወንና ሌሎች ማኅበራዊ ህይወት ውስጥ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። 

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በዓለም አቀፍ ደረጃ 970 ሚሊየን ሰዎች በተለያዩ የአዕምሮ ጤና ችግር ውስጥ መኖራቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት አመላክቷል።     

በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች በዚህ ህመም ውስጥ መኖራቸውን ነው የዘርፉ የሕክምና ባለሙያዎች የሚናገሩት። 

እንዲያም ሆኖ በአዕምሮ ሕመም ታካሚዎች ላይ የሚደርሰው መድሎና መገለል ታካሚዎች በወቅቱ እንዳይታከሙ እያደረገ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። 

በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአዕምሮ ሕመም አንድ ሰው የሚያጋጥመው የአስተሳሰብ፣ የስሜትና የባህሪ መዘበራረቅ የዕለት ተዕለት ተግባሩን በአግባቡ እንዳይከውን የሚያደርግ ነው።  

የአዕምሮ ሕመም ማንኛውንም ሰው ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ጎን ለጎንም የተለያዩ ዓይነት የአዕምሮ ሕመሞች መኖራቸውንና የአዕምሮ ሕመም በአብዛኛው ሰዎች አምራች በሚሆኑበት ወቅት የሚያጋጥም መሆኑንም ነው ያብራሩት። 


 

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና ዳይሬክተርና የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኢማኑኤል አስራት በበኩላቸው፤ በሥራ ከባቢ ለአዕምሮ ጤና ምቹ የሆነ ሁኔታን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ለአዕምሮ ጤና ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሠራተኞችን ምርታማነት የሚያሳድግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ስፔሻሊስቶቹ ጥናቶችን ጠቅሰው እንደገለጹት፤ በአዕምሮ ሕመም የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ።   

ከዚህ ውስጥ የድብርት ሕመም ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ሲሆን፤ ከባድ የሆነው የአዕምሮ ሕመም ከ 0 ነጥብ 5 እስከ 1 በመቶ እንደሚደርስ በተለያዩ ጥናቶች መመላከቱን ገልፀዋል።

ሆኖም ሕመሙ ካለባቸው 100 ሰዎች አሥሩ ብቻ ዘመናዊ ሕክምና ያገኛሉ ተብሎ እንደሚታመንና ቀሪዎቹ በባህላዊና መንፈሳዊ ሕክምና እንዲሁም ያለሕክምና በቤት ውስጥ ተደብቀውና በየጎዳናው የሚዘዋወሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።    

የአዕምሮ ጤና በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ያገኘው ትኩረት በቂ አለመሆኑን ጠቁመው፤ የባለሙያዎችና የግብዓት እጥረት በዘርፉ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ታካሚዎችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው መድሎና መገለል ታካሚዎች ሕክምናቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑንም አስረድተዋል።

መድሎና መገለሉ ታካሚዎች በወቅቱ ታክመው ከሕመማቸው እንዳያገግሙና መደበኛ ህይወታቸውን እንዳይመሩ አዳጋች ሁኔታን መፍጠሩንም ገልፀዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ ኦክቶበር 10 ቀን የአዕምሮ ጤና ቀን ታስቦ የሚውል ሲሆን፤ ዘንድሮም " በሥራ ቦታ የአዕምሮ ጤናን ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ አሁን ነው" በሚል መሪ ኃሳብ ቀኑ ታስቦ የሚውል ይሆናል። 

       

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም