የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለአሻም ሚዲያ ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለአሻም ሚዲያ ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለአሻም ሚዲያ ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
አሻም ቴሌቪዥን ጣቢያ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2013 እና ሌሎች የአገሪቱን ህጎች እንዲሁም የፈቃድ ውል ግዴታዎች አክብሮ ለመስራት ከባለስልጣኑ ፍቃድ ወስዶ በመስራት ላይ ይገኛል።
ይሁንና ጣቢያው ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን፣ ግጭት አባባሽ ዘገባዎችን፣ የሕዝብን አብሮነት የሚሸረሽሩና የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ መረጃዎችን በቂ ማጣራት እና ምክንያታዊ ጥረት ሳያደርግ በተደጋጋሚ ጊዜ ማሰራጨቱን በይዘት ክትትል ማረጋገጡን ባለስልጣኑ ገልጿል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ከዚህ ቀደም ባሰራጨው ግጭት ተኮር እና ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ በባለስልጣኑ የጽሁፍ እና የቃል ማሳሰቢያ ሲሰጠው ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ጣቢያው በባለስልጣኑ የተሰጠው የጽሁፍ እና የቃል ማሳሰቢያን ባለማክበር የአገሪቱን ሕጎች የሚጥሱ ይዘቶችን በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝ ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው።
ጣቢያው ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ በየጊዜው የሚሰራጩ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ወደ መደበኛ ሚዲያ በማምጣት ሕብረተሰቡን ለማደናገር ጥረት ሲያደርግ እንደሚስተዋል ገልጿል።
በመሆኑን የአሻም ቴሌቪዥን ጣቢያ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2013 መሰረት የሕግ የበላይነትን አክብሮ በገባው የፈቃድ ውል ግዴታ ከመስራት አንጻር በፈጸመው ተደጋጋሚ ጥሰት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተጠሰው ባለስልጣኑ አስታውቋል።