ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፔሻሊቲ ቡና አውደ ርዕይ ላይ እየተሳተፈች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፔሻሊቲ ቡና አውደ ርዕይ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፔሻሊቲ ቡና አውደ ርዕይ ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በጃፓን ስፔሻሊቲ ቡና ማህበር(SCAJ) የተዘጋጀው አውደ ርዕይ በቶኪዮ ተጀምሯል።
በጃፓን እና በላኦስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ከጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች፣ ከጃፓን ስፔሻሊቲ ቡና ማህበር ፕሬዝዳንት እና ከሌሎች ቡና ላኪ ሀገራት አምባሳደሮችና ተወካዮች ጋር በመሆን አውደ ርዕዩን አስጀምረዋል።
በቶኪዮ ‘Big Sight’ በተሰኘው የኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው የስፔሻሊቲ ቡና አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ ሰፊ ተሳትፎ እንደምታደርግ ተገልጿል።
አምባሳደር ዳባ ለኢትዮጵያ ተሳታፊዎች እና የኢትዮጵያን ቡና በማስገባት ላይ ለሚገኙ የጃፓን ኩባንያዎች ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደሩ አዳዲስ የጃፓን ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ቡና ማስገባት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተለያዩ የቡና አምራቾችና ላኪዎች ከተውጣጡ ተሳታፊዎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ቡና በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።
አውደ ርዕዩ እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ቡና አምራቾች፣ ላኪዎች እና ገዢዎች ተሳታፊ መሆናቸውን በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።