ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓትን በመተግበር ለምድራችን ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየች ነው - የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓትን በመተግበር ለምድራችን ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየች ነው - የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓትን በመተግበር ለምድራችን ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየች ነው ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓት ግንባታን ለማበረታታት ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄደውን "ኢትዮ_ግሪን ሞቢሊቲ 2024" የተሰኘ ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየም የተመለከተ የገቢ ማሰባሰቢያ ቅድመ ሁነት መድረክ የዘርፉ ተዋኒያን በታደሙበት ዛሬ ማምሻውን ተካሂዷል።
ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉ ከ10 እስከ 15 በመቶ ለአየር ብክለት መንስኤ መሆኑን ገልጸው፤ በዘላቂ የአረንጓዴ ኢክኖሚ ግንባታ ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
በዚህም ከትራንስፖርት ዘርፍ የሚወጣውን በካይ ጋዝ መቀነስና የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ወደ ስርዓቱ ማስገባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ የታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወይም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች የማድረግና ምቹ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ አበክሮ እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከተሞች የሚደረገው የዘመናዊ ከተማ ልማት ስራዎችም ለአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን አሁንም በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ የግልፀኝነት ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በዚህም የፊታችን ህዳር የሚደረገው ዓለም አቀፍ ዐውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየም ግልፀኝነትን ለመፍጠርና የዘርፉን ተዋንያን ለማነቃቃት ያለመ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ከዐውደ ርዕይነት ባሻገርም ኢትዮጵያ ለህዝቦቿም ሆነ ለምድራችን ደህንነት መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት የምታሳይበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዐውደ ርዕዩ ከ700 በላይ የአፍሪካ የዘርፉ ተዋኒያን እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፣ ይህ ለዐውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
ዐውደ ርዕዩ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካን ገበያ ታሳቢ ያደረገ ግዙፍ ሁነት እንደሆነ አንስተዋል።
በዚህም ሚኒስቴሩ ይህን ወሳኝ ዐውደ ርዕይ ስኬታማ ለማድረግ ገቢ ማሰባሰብ በማስፈለጉ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ እንደተዘጋጀ ጠቅሰዋል።
በዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለገቢ ማሰባሰብያ ንቅናቄው የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።