የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ቅድሚያ የምንሰጠው የጋራ አጀንዳችን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ቅድሚያ የምንሰጠው የጋራ አጀንዳችን ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ቅድሚያ የሚሰጡት የጋራ ጉዳይና አጀንዳ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ የጂኦ-ፖለቲካ ሁኔታና አንድምታን እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብርና የአፈጻጸም ውጤቶችን በማስመልከት ምክክር አካሂደዋል።
መድረኩን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ መርተውታል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ መለሰ ዓለሙ፤ መድረኩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ አስፈጻሚ የአቅም ግንባታ አንድ መርሃ-ግብር በሚል ስያሜ የተደረገ ነው ብለዋል።
መድረኩም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አብሮ የመሥራት ባሕል ማዳበር በሚያስችሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመሥራት ልምምድ እያደገ የመጣበት መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሃሳቦችን በማንሸራሸር የጋራ ግንዛቤ የሚያዝበት መሆኑን ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃሳብ፣ የአመለካከትና የፖለቲካ አጀንዳ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር በመምከር የአቅም መገንቢያ መድረክ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ገለፃና ማብራሪያ መስጠታቸውን አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው ሀገር በቀል የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብር ትግበራን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
በመድረኩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ጥያቄ፣ ሃሳብና አስተያየት በማቅረብ በጋራ መሥራትና መቆም በሚገባ ጉዳዮች ላይ መግባባትና ግንዛቤ የተፈጠረበት መሆኑን አስታውቀዋል።
የዕለቱ መድረክም በወቅታዊ ሀገራዊ የሰላም፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቦ በተነሱ ሃሳቦች ላይ መግባባት መደረሱን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ መድረኩ የመንግስትና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንኙነት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊነትን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
በወቅታዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች እንዲሁም የኢትዮጵያን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ መርሃ-ግብር የአፈጻጸም ሂደት ላይ የተሻለ መግባባትን የፈጠረ ማብራሪያ የተሰጠበት መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮ-ሶማሊላንድ መካከል የተደረገው የባሕር በር ስምምነትም ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተነስቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን፤ መድረኩ የአስተሳሰብና ፍላጎት ልዩነት ያነገቡ ፓርቲዎች አንኳር በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር የሚሰሩበትና የፖሊሲ አማራጭ ለማቅረብ የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል።
የፖለቲካ አደረጃጀቶች ያሏቸውን ለሀገር የሚበጁ ሃሳቦች ተመራጭ እንዲሆኑላቸው ግፊት ማድረጋቸው የሚጠበቅ ቢሆንም በሀገር ሉዓላዊነት፣ የህዝብ ደኅንነትና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ተባብረን የምንደግፋቸው ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ ካሉት አሥር መርሆች መካከል የሀገር ሉዓላዊነት፣ የህዝብ ደኅንነትና የብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናው ግዙፍ ሀገር ሆና ሳለ በታሪክ ስብራት አጋጣሚ ያጣችውን የባሕር በር ባለቤትነት ለመመለስ የዚህ ትውልድ የህዝብ አጀንዳ ማድረጉን አስገንዝበዋል።
መድረኩ የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅምና መረጋጋት የማያሳስባቸው አንዳንድ ኃይሎች ረዥም እጃቸውን በቀጣናው ለማስገባት የሚያደርጉትን ጥረት በመገንዘብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በጋራ የመከላከል አቋም እንድንይዝ አስችሎናል ብለዋል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሙሳ አደም፤ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ሰላማዊ አማራጭን በመከተል ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ሲነሳ የቆየ ጉዳይ ላይ ምክክር መደረጉን ገልፀዋል።
በሌላ በኩልም በሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብር ላይ በውጭ ምንዛሬ፣ በብድር፣ በዓመታዊ በጀት፣ በገቢ ዕድገት፣ በውጭ ሀገር የብድር አገልግሎት ሥርዓትና ሁኔታ ላይ ጥልቅ ምክክር በማካሄድ መግባባት የተፈጠረበት ነው ብለዋል።