ኢትዮጵያ በኮፕ 29 ጉባዔ ላይ ቅድሚያ ሰጥታ የምታቀርባቸውን ቁልፍ የትኩረት መስኮች ይፋ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በኮፕ 29 ጉባዔ ላይ ቅድሚያ ሰጥታ የምታቀርባቸውን ቁልፍ የትኩረት መስኮች ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአዘርባጃን ባኩ በሚካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) ላይ የምታቀርባቸው ቁልፍ የትኩረት መስኮች ይፋ አድርጋለች።
አረንጓዴ አሻራ እና የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ከትኩረት መስኮቹ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ፍሬዲ ስቫን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ዴንማርክ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ያላቸውን የጋራ ትብብር እና ጥረቶች ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
አቶ ስዩም ዴንማርክ ኢትዮጵያ በአዘርባጃን ባኩ ከሕዳር 2 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) ለሚኖራት ተሳትፎ እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
አገራቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መጻኢ ጊዜ ለመፍጠር በተለይም በደን ልማት ላይ ያላቸውን የጋራ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ዴንማርክ ከኮፕ 29 ጉባዔ ጎን ለጎን ሌሎች የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች እንደሚያዘጋጁም ጠቁመዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ከአምባሳደር ፍሬዲ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ በኮፕ 29 ቅድሚያ ሰጥታ የምታቀርባቸውን የትኩረት መስኮች አብራርተዋል።
አረንጓዴ አሻራ፣ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን የሚቀንሱ ዘላቂ እና ስማርት ከተሞችን መገንባት እና የኤሌክትሪክ መኪናዎች የተመለከቱ የፖሊሲ እርምጃዎች ከትኩረት መስኮቹ በዋናነት ይጠቀሳሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ፍሬዲ ስቫን ኢትዮጵያ በኮፕ 29 ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ከዴንማርክ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦች ጋር የተጣጣሙ ናቸው ብለዋል።
ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና የከባቢ አየር ጉዳዮች ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግም ገልጸዋል።
አምባሳደር ፍሬዲ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ጥምረት (Alliance of Negative Emitters) እንድትቀላቀል ጠይቀዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ኢትዮጵያ ጥምረቱን በመቀላቀል የበኩሏን ሚና መወጣት እንደምትፈልግ ገልጸው ሀገሪቷ አረንጓዴ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መጻኢ ጊዜ ለመፍጠር ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዴንማርክን ጨምሮ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ግቦች እውን የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን የመፍጠር ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።