ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስታዲየሞች የካፍ እና የፊፋ መመዘኛ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ እና ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው- አምባሳደር መስፍን ቸርነት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ስታዲየሞች የካፍ እና የፊፋ መመዘኛ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ እና ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።

ክለብ ላይሰንሲንግ አሠራር ሥርዓት በሴቶች እግር ኳስ ጭምር ተግባራዊ መሆኑ በካፍ እውቅና እንደተሰጠው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የካፍ እና የፊፋ መመዘኛዎች ያሟላ ስታዲየም አለመኖሩ ግን ተጨማሪ ወጪ በማስወጣቱና በጨዋታ ውጤት ረገድም ትልቅ ችግር ሆኖ ቀጥሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚፈለገውን ውጤት እያመጣ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ብሔራዊ ቡድኑ የተሻለ ውጤት እንዲያገኝ የጋራ ጥረትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ክለቦች ለክለብ ላይሰንሲንግ አሠራር ተገዢ በመሆንና የሴቶችና የታዳጊ ቡድኖች በማቋቋም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ለታዳጊዎች እግር ኳስ ልማት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የካፍ እና ፊፋ መመዘኛን ያሟሉ ስታዲየሞች እንዲኖሯት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና መንግሥት በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ እንዲሆን በጋራ መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።

ፌዴሬሽኑ ጤናማ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን ማጎልበት እንደሚገባው ጠቅሰው፤ የሴቶች እግር ኳስ እድገት እንዲጎለብት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የስፖርታዊ ጨዋነት ማስፈን፣ የታዳጊ እና ወጣቶች ልማት እንዲሁም የውድድሮች መርኃ-ግብር አወጣጥ ትኩረት እንደሚያሻቸው ነው የጉባዔው ተሳታፊዎች ያነሱት።

ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጠቅላላ ጉባዔ አባል እንዲሆን የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በጉባዔው ጸድቋል።

ክልሉ የጠቅላላ ጉባዔው አባል የሆነው አዲስ የተቋቋመ ክልል በቀጥታ የጉባዔው አባል ይሆናል በሚለው የአሠራር ደንብ አማካኝነት ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 ዓ.ም የዕቅድ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በሪፖርቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2016 በጀት ዓመት ከ186 ሚሊየን 757 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱና ከ214 ሚሊየን 90 ሺህ በላይ ወጪ ማውጣቱ ተመላክቷል።

በበጀት ዓመቱ ለወንዶች እና ሴቶች ታዳጊ እና ዋና ብሔራዊ ቡድኖች ከ96 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም