ቀጥታ፡

የግብፁ ኢጅፕት ኢንዲፔንደንት በህዳሴ ግድብ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ይችላል በሚል ያሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦የግብፁ ኢጅፕት ኢንዲፔንደንት (Egypt Independent) በህዳሴ ግድብ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ይችላል በሚል ያሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ጅኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በዓለም ላይ የስምጥ ሸለቆ የሚያልፍባቸው፣ አካባቢዎች ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ናቸው።

በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ከሚያልፍባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ፈንታሌ በአይነቱ ቀላል የሚባል በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 9 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ሰሞኑን መከሰቱ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎም የግብፁ ኢጅፕት ኢንዲፔንደንት (Egypt Independent) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ይችላል የሚል የተሳሳተ መረጃ አሰራጭቷል።

የኢትዮጵያ ጅኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢጃራ ተስፋዬ፤ በህዳሴ ግድብ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያጋጥም ይችላል በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።


 

ዋና ዳይሬክተሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከስምጥ ሸለቆ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ ሲገነባ የመሬት መንቀጥቀጥና ሌሎች የሥነ ምድር አደጋዎችን ታሳቢ ያደረገ ጥናት የተካሄደበት መሆኑን ገልጸዋል።

የተደረገው ጥናትም የህዳሴው ግድብ የሥነ ምድር አደጋ ስጋት እንደሌለበትና የተሻለ ቦታ ላይ እንደሚገኝ የሚያመለክት ነው ብለዋል።

በስምጥ ሸለቆ አካበቢ የሚከሰተው የሥነ ምድር አደጋ በሌሎች አካባቢዎች ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳይ ጥናት አለመኖሩንም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ በተለይ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሥነ ምድር አደጋዎች ቢከሰቱም የህዳሴው ግድብ በሚገኝበት አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ የታየበት ዘመን የለም ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ ጥልቅ የሥነ ምድር ጥናት የተደረገበት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ሥጋት አለበት የሚለው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኢጅፕት ኢንዲፔንደንት ያሉ ሚዲያዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ መሰል መሰረተ ቢስ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ማየት የተለመደ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም