የመንግስት የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጠቅብንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጠቅብንን ለመወጣት ዝግጁ ነን
ቦንጋ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፡-የመንግስት የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ትናንት ሲካሄድ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው መሰየማቸው ይታወሳል።
በዚሁ ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የመንግስትን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ ሪፖርትና የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች በፕሬዚዳንቱ የቀረቡ ዋና ዋና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አየለ ሀይሌ እንዳሉት አዲሱ ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር በተለይ ለሀገር ሰላምና አንድነት መጠበቅ መንግስት የሰጠው ትኩረት ተገቢና ወቅታዊ ነው።
መንግስት በመነጋገር ችግሮችን በሰለጠነ አግባብ ለመፍታት የሰጠው ትኩረት ተገቢ መሆኑን አንስተው፣ ለስኬቱ የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
አዲሱ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ያበረከቱና የካበተ ልምድ ያላቸው መሆኑን አቶ አየለ አስታውሰው፣ በቀጣይም በተሰጣቸው ሃላፊነት የተሻለ ሥራ ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።
በ2016 በብዙ ዘርፎች እንደ ሀገር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ከፕሬዚዳንቱ ገለጻ መረዳታቸውን የጠቀሱት አቶ አየለ፣ በቦንጋ ከተማም ተጨባጭ የልማት ሥራዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በየዘርፉ ውጤቶችን በማጠናከር መንግስት ለ2017 በጀት ዓመት የተያዙ አቅጣጫዎችን ስኬታማ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸው፣ ለዚህም ሁሉም ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ አብርሀም አባተ በበኩላቸው የትላንቱን የፓርላማ ውሎ መከታተላቸውንና የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየሰፋ መሆኑንን መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ከአዲሱ ፕሬዚዳንት የፓርላማ መክፈቻ ንግግር በማህበራዊ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በቴክኖሎጂ ሀገርን ለማሻገር የሚያስችሉ ድሎች እንደተመዘገቡ መረዳታቸውን ተናግረዋል።
በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የተመዘገቡ ውጤቶችን ዘንድሮም ለማስቀጠልና ላልተፈቱ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።
በየዘርፉ የተገኙ ውጤቶች እንዲጠናከሩ መንግስትና ህዝብ ተባብረውና ተናበው መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ለዚህም የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አየለ ወልደገብርኤል በበኩላቸው አዲስ የተሾሙት ፕሬዚዳንት ለሀገር የጎላ ፋይዳ እንደሚያበረክቱ ገልጸው፣ ከእሳቸው ብዙ እንጠብቃለን ብለዋል።
በፕሬዚዳንቱ ንግግር በልማትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ወጤቶች በአይን የሚታዩና ተጨባጭ መሆናቸውንም አቶ አየለ አንስተዋል።
በተለይ ሰላምን ለማስፈንና የኑሮ ውድነትን ለማርገብ በፕሬዚዳንቱ የቀረቡ የመንግስት አቅጣጫዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በሚችሉት የራሳቸውን አስተዋጾ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
መንግስት በተለይ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማርገብና ለዘላቂ ሰላም የጀመራቸውን ሥራዎች እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።