የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ3 አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ3 አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሔደው 4ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባ በ3 አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ካቢኔው ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ፡-
1ኛ. የኮሪደር ልማት የግዥ ጥያቄ፣ የግንባታ በጀት እና የግዢ ሂደት አወሳሰን በተመለከተ በፋይናንስ ቢሮ በኩል ለቀረበለት ጥያቄ፤ ለልማቱ መሳለጥ እና የሀብት መባከን እንዳይፈጠር እንዲሁም የሥራ ቅልጥፍናን በሚጨምር መንገድ ለመስራት እንዲያስችል የሚያደርግ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተወያይቶ አፅድቋል::
2ኛ. በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የሚተዳደሩ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አያያዝ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም እና ወደ ከተማው ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተዳደር ዘይቤ ማምጣት እንዲያስችሉ ተቋማቱ በትምህርት ቢሮ ይዞታ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገቡ የሚያስችላቸው ደንብ አስፈላጊ በመሆኑ አፅድቋል።
3ኛ. የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰው ኃይል ስምሪት በማዕከል፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ለማመጣጠን እንዲቻል በተዘጋጀው የዝውውር እና ምደባ ረቂቅ ደንብ በየተቋማቱ ያለውን የሰው ሀብት በውጤታማነት ለመጠቀም እንዲቻል የሚያግዝ በመሆኑ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።