የክልሎችን የበጀት ድጎማ ቀመር በመረጃ ላይ ተመስርቶ ማሻሻያ የማድረግ ዕቅድ ተይዟል- አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎችን የበጀት ድጎማ ቀመር በመረጃ ላይ ተመስርቶ ማሻሻያ የማድረግ ዕቅድ ተይዟል- አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦የክልሎችን የበጀት ድጎማ ቀመር በመረጃ ላይ ተመስርቶ ማሻሻያ የማድረግ ዕቅድ መያዙን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ እና የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎችን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፅድቋል።
የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የቀመር ማሻሻያ ማድረግም በዕቅዱ አፅንዖት የተሰጠው መሆኑ ተመላክቷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ ቋሚ ኮሚቴው ቀመር ማሻሻልን በአጽንዖት ማየቱ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የክልሎችን የበጀት ድጎማ ቀመር በመረጃ ላይ የተመሠረተ ማሻሻያ ለማድረግ መታሰቡን ጠቁመዋል።
ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ስታትስቲክስ ባለሥልጣንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት የሚደረግ መሆኑን አፈ-ጉባዔው አንስተዋል።
በዚህ ረገድ የሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች መረጃ እንዲያደራጁ አቅጣጫ መሰጠቱንም ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ በተመሳሳይ የማንነት አስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይቷል።
የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምንና የነበሩ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሥራ በዝርዝር የታቀደ እንደሆነ ተገልጿል።
የምክር ቤት አባላትም የቀረበውን ዕቅድ በማንነትና አስተዳደር ወሰን ላይ የቀረቡና ምላሽ የተሰጠባቸው እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች የተቃኙበት አግባብ ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተዋል።
የማንነት አስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ፍቅሬ አማን፤ የማንነትና የወሰን ጥያቄ በአንድ ጊዜ የሚመለስ ባለመሆኑ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመሥራት በዕቅዱ መካተቱን አስረድተዋል።
የሰላምና መረጋጋት ችግርን የሚፈታ ብሔራዊ የግጭት መከላከልና የሰላም ግንባታ ስትራተጂ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ በሰጡት ማብራሪያም የማንነትና አስተዳደር ወሰን ጉዳዮችን በህገ-መንግስቱ መሠረት ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው ከመንግሥታት ግንኙነት የዴሞክራሲ አንድነትና የህገ-መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ፤ ከህገ-መንግስት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ከህገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል የቀረበለትን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ አፅድቆታል።
ከህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል ውሳኔ በተሰጣቸውና በህገ-መንግስት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን ውሳኔ ሀሳብም መርምሮ አጽድቋል።
የህገ-መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ በተሰጣቸውና ለምክር ቤቱ በይግባኝ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ከቋሚ ኮሚቴው የቀረበ የውሳኔ ሃሳብንም አፅድቋል።
በሌላ በኩል የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢና ጸሐፊን በተመለከተ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አሻድሊ ሐሰን እንዲሁም የህገ-መንግስት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ፍሬህይወት ዱባለ እንዲሆኑም ከአፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የቀረበለትን ሃሳብ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።