እየጨመረ ያለውን የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድን ማስተናገድ የቻሉ የሎጅስቲክስ የሪፎርም ስራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
እየጨመረ ያለውን የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድን ማስተናገድ የቻሉ የሎጅስቲክስ የሪፎርም ስራዎች ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ):- እየጨመረ ያለውን የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድ መጠን ማስተናገድ የሚችል የሎጅስቲክስ አቅምን ለማሳደግ በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተከናውነው ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት በሎጂስቲክስ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላት በተዘጋጀው የእውቅና መርሃ-ግብር ላይ ነው።
በንግግራቸውም እየጨመረ ያለውን የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድ መጠን ማስተናገድ የሚችል የሎጅስቲክስ አቅምን ለማሳደግ በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተከናውኗል ብለዋል።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አካል የሆነው የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ እና ፖሊሲ ትግበራ ከተጀመረ 5 አመታትን ማስቆጠሩን ገልጸው እስካሁን ባለው ሁኔታ በስትራቴጂው ከተለዩ የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ ከ53 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተግባራዊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ በራስ አቅም በገለልተኛ አካል የተካሄደ ሀገራዊ የሎጂስቲክስ አፈፃፀም ጥናት የቀረበ ሲሆን በጥናቱ ግኝት መሠረት የሎጂስቲክስ አፈፃፀም በልኬቱ መሠረት የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህም ባሻገር የሎጂስቲክስ አፈፃፀም ስኬቶችና ተግዳሮቶች ላይ የፓናል ውይይት መካሄዱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና ሌሎችም የሎጂስቲክስን አፈፃፀም ለማሳደግ የአሰራር፣ የህግ ማዕቀፍ እና በሌሎች በቀጣይ መንግስት በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ሀሳብ ማቅረባቸውም ተጠቁሟል።
በመጨረሻም በሎጂስቲክስ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የዘርፉ ተዋናዮች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ-ግብር መካሄዱንና የሀገር መከላካያ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር፣ ጥቁር አባይ የጭነት ትራንስፖርት እና ሌሎችም እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡