የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና ማስቀጠል የሚችል አስተማማኝ የሰላም ሀይል ማፍራት ተችሏል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017 (ኢዜአ)፡- የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና ማስቀጠል የሚችል አስተማማኝ የሰላም ሀይል ማፍራት ተችሏል ሲሉ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቢሾፍቱ የዝግጁነት ማረጋገጫ ማዕከል ተገኝተው በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ኦቨር ሆል ተደርገው የተዘጋጁና በመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ በሞድፊኬሽን ተሻሽለው የተሰሩ የሰራዊቱን የግዳጅ አፈፃፀም የሚያሳልጡ የሚካናይዝድ ትጥቆችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

ሰራዊቱ ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር የሚለውን የተቋሙን እሴት መሠረት በማድረግ መተኪያ ለሌላት ህይወቱ ሳይሳሳ መስዋእትነትን እየከፈለና ሰላምን እያረጋገጠ የሚገኝ የህዝብ ዋልታና መከታ መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተቋሙ የሚሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በእቅዳችን መሰረት ያለምንም እንቅፋት መወጣት የሚችል አስተማማኝ ሀይል አፍርተናል፤ በቀጣይም የውስጥ አቅምን በመጠቀም ወጭ ቆጣቢነትን ባማከለ መልኩ የሰራዊታችንን የዝግጁነት ደረጃ ይበልጥ የሚያረጋግጡ መሰል ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

እነዚህ የዘመኑና የሰራዊቱን የማድረግ አቅም በእጅጉ የሚያጎለብቱ ትጥቆች ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ተሻሽለው የተሰሩ ሲሆኑ ቀድሞ ወደነበሩበት የምስራቅ ዕዝ ሜካናይዝድ ክፍሎች ሲመለሱ የሠራዊቱን ክንድ የሚያፈረጥሙ ተጨማሪ አቅሞች እንደሚሆኑም ገልፀዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በርካታ የተቋሙን ተልእኮዎች በማቀድና በመምራት በኩል ከፍተኛ ስራ ለሰራው ለመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንና ለመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ሰራዊቱም በየጊዜው የሚታጠቃቸውን ትጥቆች በጥንቃቄና በእንክብካቤ በመያዝና በማቆየት እንዲሁም ለታለመላቸው አላማ ብቻ በማዋልና እንደተቋምም የሀገራችንን እድገት በማስቀጠል በኩል የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርብናል ነው ያሉት።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ በትጥቅም ሆነ በስነ-ልቦናዊ ዝግጁነቱ ያለውን አቅም በማሳደግ እንደወትሮው ሁሉ ለሀገር ሰላምና ለህዝብ ደህንነት በትኩረት መስራት ይኖርበታል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም