በቢሾፍቱ ከተማ በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 16 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ቦታ በጥራትና በፍጥነት ማልማት ተችሏል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦ በቢሾፍቱ ከተማ በመጀመሪያው ምዕራፍ  የኮሪደር ልማት 16 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ በጥራትና በፍጥነት ማልማት መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በ2016 ዓ.ም ከተሞችን የብልጽግና ማዕከላት ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በመላው አገሪቱ መስፋፋቱን በመጥቀስ በወላይታ፣ ደሴ፣ ሻሸመኔ፣ አርባ ምንጭ፣ ነቀምቴ፣ ባህርዳርና አዳማን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ልማቱ መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደበሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በ 11 መስመሮች 96 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን የኮሪደር ልማት በተለያዩ ምዕራፎች ለማከናወን በማቀድ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡


 

የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአራት ወራት በፊት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ 16 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ፣የእግረኛና የብስክሌት መንገድ እንዲሁም  የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

እንደዚሁም በ50 ሄክታር መሬት ላይ የደንና የአረንጓዴ ልማት ስራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

በሁለት አመት ውስጥ አጠቃላይ የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለነዋሪዎቿ የተመቸች፤ ቱሪስቶችን የምትስብ ከተማ የማድረግ ግብ መያዙን ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ የመስህብ ጸጋ በማልማት የቱሪስት መዳረሻነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

የኮሪደር ልማት ስራው የከተማ አስተዳደሩን ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት የመምራት አቅም እያሳደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በልማት የተነሱ ነዋሪዎች መብታቸው ተጠብቆ ተገቢው ካሳና ምትክ ቦታ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በኮሪደር ልማት ስራው ህብረተሰቡ እያደረገው ያለው ተሳትፎ አበረታች መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው በቀጣይ የከተማው ህዝብ ቀና ትብብርና ድጋፉን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል ።

የመጀመሪያውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እስከ ጥር 30 ቀን 2017 ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነና ሁለተኛውን ምዕራፍ ደግሞ በተጀመረ በሁለት ወር ለመጨረስ መታቀዱን ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም