የሃይማኖት አባቶች ትውልድን በመልካም ስነ ምግባር የማነጽ ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች ትውልድን በመልካም ስነ ምግባር የማነጽ ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
ጎንደር ፤ መስከረም 28/2017 (ኢዜአ)፡- የሃይማኖት አባቶች ትውልድን በመልካም ስነ ምግባር በማነጽ ለዘላቂ ሰላም መስፈን እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ።
በሰላም እሴቶች ዙሪያ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አድባራትና ደብሮች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ከርስቲያን መሪዎችና አስተዳዳሪዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
በዚህ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደተናገሩት፤ የቀደሙ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና መሪዎች ትውልዱን በስነ ምግባር በማነፅ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል፡፡
ላቅ ባለ የሞራል ስብዕና ላይ የተገነባ ትውልድ አገርን ከችግር የማሻገር አቅምና ብቃት እንዳለው ጠቅሰው፤ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለሰላም ለአብሮነት በመጠቀም ትውልድን ማነጽ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የሰላም ትውልድ በመገንባት ትልቅ ድርሻና ሃላፊነት እንዳለባት ጠቁመው፤ የሃይማኖት አባቶች ለሰላም ዋጋ በመስጠት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
የሰው እገታ ወንጀሎች የከተማውን መልካም ስምና ገጽታ ያጎደፉ መሆናቸውን አንስተው፤የሃይማኖት አባቶች ይህንን ድርጊት በማውገዝ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ለከተማው ዘላቂ ሰላም እውን መሆን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ የሕግ ማስከበር ስራውን በማጠናከር በከተማው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ህሩያን ቆሞስ አባ ዮሴፍ ደስታ በበኩላቸው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጆች ስለሰላም ማስተማርና መስበክ የዘወትር ተግባሯ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
''አሁን ላይ በከተማው የሰፈነው ሰላም የእለት ተእለት ሃይማኖታዊ የፀሎት ስርዓት በአግባቡ ለማከናወን አግዞናል'' ያሉት ደግሞ ቄስ አስካለ ጥበቡ ናቸው፡፡
''የሰላም እሴቶች የሆኑትን አብሮነትና ወንድማማችነትን በማጠናከር እኛ የእምነት አባቶች ለአገራችንና ከአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻችንን ለማበርከት ዝግጁ ነን'' ብለዋል፡፡
በመድረኩ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ አድባራትና ደብሮች የተውጣጡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አስተዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በሰላም እሴቶችና ተግባራት ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።