ቀጥታ፡

በቡና ዘርፍ የላቀ አበርክቶ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ):-በቡና ዘርፍ የላቀ አበርክቶ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ቡና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ 

የእውቅና መርሐግብሩ  ''ቡናችን ለብልጽግችን " በሚል መሪ ሐሳብ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ ም በሳይንስ ሙዚየም እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡ 

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የዕውቅና መርሐ ግብሩን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።  

በመግለጫቸውም ባለፈው በጀት ዓመት 300 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ አገር ገበያ ተልኮ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው፤ ይህም በታሪክ ከፍተኛ ገቢ መሆኑን አመልክተዋል።  

በዓለም አቀፍ የልዩ ጣዕም ውድድር የኢትዮጵያ ቡና አሸናፊ በመሆን አንድ ኪሎ ግራም ቡና በ103 ሺህ ብር በመሸጥ ከፍተኛ ዋጋ ሆኖ መመዝገቡን አያይዘው ገልጸዋል።  

በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች ስኬቶች እንዲመዘገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ  አርሶ አደሮች፣ ላኪዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያንና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በሚገኙበት በብሔራዊ ሳይንስ ሙዚየም ከነገ በስተያ እውቅናው እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡  

በእውቅና መርሐ ግብሩም ላይም በከፍተኛ ደረጃ የኢትዮጵያን ቡና የገዙ የተመረጡ ሶስት አገራት እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።  

ለመርሐ ግብሩ ስኬት  ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቡና ማህበር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበርና ሌሎችም በጋራ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡   

መርሐ ግብሩ ለንግዱ ማህበረሰብ  የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ እንደሚሆንም ይጠበቃል ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም