የኮሪደር ልማት ዋና አላማው ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት ዋና አላማው ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦ የኮሪደር ልማት ዋና አላማው ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፤ ገጽታዋን ማሻሻልና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ከመንግስት እና ከግል ሚድያ ጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠታቸውን ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተሰጠን የስራ መመሪያ መሰረት የሁለተኛ ዙር ኮሪደሮች ስምንት ሲሆኑ፣ ለህዝብ ያለእረፍት እየሰራን ከህዝብ የምንደብቀው ምንም ስለሌለ በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቻለሁ ብለዋል።
ማብራሪያ መስጠቱ ለወደፊትም ይቀጥላል ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ዋና አላማው ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፤ ገጽታዋን ማሻሻል እና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነውም ብለዋል።
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በአጠቃላይ 2,817 ሄክታር መሬት በሚሸፍን እና 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው ቦታ ላይ የሚገነባ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በግንባታ ስራው ከተካተቱ የመሰረተ ልማት ስራዎች ውስጥ የመንገድ ግንባታ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች ግንባታ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ የታክሲና አውቶቢስ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የህዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች፣ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ መብራት፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት እንዲሁም የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች ዝርጋታ ስራ ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ስራው በዋናነት በከተማው አቅም እና በጀት የሚከናወን መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፤ የመብራት አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በዚህ ውስጥ መሰረተ ልማታቸውን በመዘርጋትና ከተማዋን ስማርት ሲቲ በማድረግ በኩል ትልቅ እገዛ የሚያደርጉ ይሆናል ብለዋል።
ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
በመልሶ ማልማት ሲኖሩ ከነበሩበት ለመኖር ምቹ ያልሆነ ጎስቋላ አካባቢዎች ለተነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶችን፣ በቂ የመስሪያ ሼዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም ከ500 በላይ የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን ለነዋሪዎቻችን ዝግጁ አድርገናልም ነው ያሉት።
በተመሳሳይ ምትክ መሬት እና ካሳ መዘጋጀቱንም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።
በሁለተኛ ዙር የተለዩት ኮሪደሮች:-
1. ካሳንቺስ- እስጢፋኖስ-መስቀል አደባባይ- ሜክሲኮ- ቸርችል-አራት ኪሎ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራ(የኮሪደሩ ርዝመት 40.4 ኪ/ሜ)
2. ጫካ ፕሮጀክት(ሳውዝ ጌት) - መገናኛ - ሃያ ሁለት- መስቀል አደባባይ ኮሪደር(የኮሪደሩ ርዝመት 7.1 ኪ.ሜ)
3. ሲኤምሲ - ሰሚት - ጎሮ- ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደር እና የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል ኮሪደር(የኮሪደሩ ርዝመት 10.8 ኪ.ሜ)
4. ሳር ቤት - ካርል አደባባይ - ብስራተ ገብርኤል - አቦ ማዞሪያ - ላፍቶ አደባባይ - ፉሪ አደባባይ ኮሪደር(የኮሪደሩ ርዝመት 15.9 ኪ.ሜ)
5. አንበሳ ጋራዥ- ጃክሮስ- ጎሮ ኮሪደር(የኮሪደሩ ርዝመት 3.1 ኪ.ሜ)
6. አራት ኪሎ - ሽሮ ሜዳ - እንጦጦ ማርያም - እጽዋት ማዕከል ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 13.19 ኪ.ሜ)
7. ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ኮሪደር(የኮሪደሩ ርዝመት 20 ኪ.ሜ)
8. እንጦጦ -ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር(የኮሪደሩ ርዝመት 21.5 ኪ.ሜ)
ከላይ የተዘረዘሩ ኮሪደሮችን ምዕራፍ በምዕራፍ ከፍለን በጥራት እና በፍጥነት እንሰራለንም ብለዋል ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው።
የከተማችን ነዋሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የትራፊክ መጨናነቅን ጨምሮ የሚኖሩ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችን በመቻል እንደ መጀመሪያው ዙር በትብብር ከተማችንን በጋራ እንድንገነባ አደራ እላለሁ ብለዋል።