ቀጥታ፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት የፈጠራ ማዕከል የሆነች አፍሪካን እንፈጥራለን- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የፈጠራ ማዕከል የሆነች አፍሪካን እንፈጥራለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ "አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማላቅ" በሚል መሪ ሀሳብ ላይ አትኩሮቱን ባደረገው 3ኛው የፓን አፍሪኮን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጉባኤ ላይ መታደማቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ጉባኤው ትብብሮች የሚጠናከሩበት እና ችግር ፈቺ ሀሳቦች የሚፈልቁበት በመሆኑ አፍሪካዊ አንድነትን በማምጣቱ ረገድ የሚኖረው ሚና የላቀ ነው ብለዋል፡፡

አፍሪካ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ መሆን እንደሌለባት ጠቅሰው፤ ይልቁኑ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አብዮት ውስጥ ግንባር ቀደሟ አህጉር ለማድረግ መስራት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ይህ የእኛ ጊዜ ነው፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ያለውን የለውጥ ሃይል በመጠቀም የአህጉራችንን መንገድ ማስተካከል ይገባናል ብለዋል ፡፡

ይህንን ጉባኤ በማዘጋጀት ረገድ ቁልፍ ሚና ለተወጡት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሠራተኞችም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም