ፕሬዝዳንቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅም ያላቸው ናቸው - የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንቱ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅም ያላቸው ናቸው - የምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017 (ኢዜአ)፦ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሰሩት የማይረሳው ሥራ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ማሳያ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በትላንትናው ዕለት ተካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሰይመዋል።
ሹመታቸውን አስመልክቶ ኢዜአ ካነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት መካከል ደሳለኝ ኤርሶ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች ለኢትዮጵያ ህልውና የቆሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲታገሉ የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ተሰማርተው ያገለገሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ አሁንም አገርን አንድ የሚያደርግና የሚገነባ ሥራ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ጨምረው ገልፀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የምክር ቤት አባል ከፈና ኢፋ( ዶ/ር) ፕሬዝዳንት ታዬ በተለያዩ መድረኮች የኢትዮጵያ ባለውታ መሆናቸውን ያስመሰከሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው መሆኑንና ኢትዮጵያን ማሻገር የሚችሉ ትክክለኛው ሰው ናቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ባላቸው ሰፊ ልምድ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችላቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከማል ሀሽም ናቸው።
ሂደቱም ያለውን የሰከነ ፖለቲካ እና አገልጋይ መሪዎችን ወደፊት የማምጣት ሥራ በተግባር ያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።