አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለማላቅ በጋራ መሥራት አለብን- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለማላቅ በጋራ መሥራት አለብን- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለማላቅ በጋራ መሥራት አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
3ኛው የፓን አፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፍረንስ "አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማላቅ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ኮንፍረንስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ተገኝተዋል።
በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ ወጣት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በኮንፈረንሱ ላይ ተሳትፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኮንፍረንሱ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፤ የአፍሪካን የተሻለ ጉዞ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማቃናት የምንችልበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለጤና፣ ለግብርና እና ሌሎችም ዘርፎች ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሯን አንስተዋል።
ዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ ለቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።
አፍሪካውያን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ በጋራ በመረባረብ የተሻለች አህጉርን መፍጠር አለብን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፤ ኮንፍረንሱም ለተሻለ የጋራ ነገ ቃላችንን የምናረጋግጥበት ነው ብለዋል።
አፍሪካውያን ሀገር በቀል እውቀቶቻቸውን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በማናበብ የተሻለ ነገርን መፍጠር እንዳለባቸውም አንስተዋል።
አፍሪካውያን ቴክኖሎጂን በማወቅ በዓለም ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አህጉራዊ አቅሞችን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።
ፈተናዎችን በጋራ መሻገር፣ በዘርፎች መካከል ትስስር መፍጠርና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በኮንፍረንሱ ላይ እንዳሉት፤ የአፍሪካን እድገት እውን ለማድረግ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የዘመኑ ወሳኝ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረት ራሱን የቻለ ተቋም መመስረቷን ጠቅሰው፤ ከሀገር አልፎ አህጉራዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለመጨመር በጤና፣ በምርምርና ሕክምናው ዘርፍ ሥር-ነቀል ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በዘርፉ ክህሎት ያላቸውን ሙያተኞች ለማፍራት ተከታታይ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኮንፍረንሱ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተመለከተ በርካታ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።