ስታዲየሞች የካፍ እና የፊፋን መስፈርት ያሟሉ እንዲሆን ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው -አምባሳደር መስፍን ቸርነት - ኢዜአ አማርኛ
ስታዲየሞች የካፍ እና የፊፋን መስፈርት ያሟሉ እንዲሆን ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው -አምባሳደር መስፍን ቸርነት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ):- መንግስት ስታዲየሞች የካፍ እና የፊፋ መስፈርት መመዘኛ ያሟሉ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 16ኛው ጠቅላላ ጉባዔውን በአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ይገኛል።
በጉባዔው ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ፣ የፌደሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች እና ሌሎች የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተገኝተዋል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት መንግስት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲለሙና እንዲስፋፋ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ይሁንና አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች አለመኖራቸው የስፖርቱ ትልቁ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።
ስታዲየሞች የካፍ እና የፊፋ መመዘኛ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ እና ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ የፌደራል መንግስት ከክልሎች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግስት የአዲስ አበባ እና የብሔራዊ (አደይ አበባ) ስታዲየሞች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ አስፈላጊውን ክትትል እያደረገ መሆኑን ነው አምባሳደር መስፍን የገለጹት።
ስታዲየሞች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ የማድረግ ተግዳሮት የቆየ ፈተና በመሆኑ በሚፈለገው ፍጥነት ስራውን ለማስኬድ አለመቻሉን ጠቅሰዋል።
መንግስት የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት ስታዲየሞች ደረጃቸውን እንዲያሟሉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮችን በዘመናዊ አሰራር ለመፍታት የተጀመረው መልካም ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ረገድ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ስፖርታዊ ጨዋነት እና ጤናማ የፋይናንስ ስርዓትን ማስፈን እንዲሁም የታዳጊ እና ወጣቶች ስፖርት ልማት በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ተቋርጦ የነበረው የካፍ ዲ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠና መጀመሩ እንደ ትልቅ ውጤት እንደሚታይ ተናግረዋል።
የካፍ የሲ እና የዲ ላይሰንስ ስልጠናዎች መጀመራቸው እየጨመረ የመጣውን የስልጠና ፍላጎት ለመመለስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የክለቦች አደረጃጀት በዘመናዊ አሰራር እንዲደገፍ ልማዳዊ የክለቦች ላይሰንስ አሰጣጥን በማስቀረት የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ በመተግበር የተሻለ ውጤት መገኘቱንና ይህን ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉት አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን አብራርተዋል።
የክለብ ላይሰንሲንግ አሰራር ስርዓት በሴቶች እግር ኳስ ውስጥ ተግባራዊ መሆኑ በካፍ እውቅና እንደተሰጠው ተናግረዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ የካፍ እና የፊፋ መመዘኛዎችን ያሟላ ስታዲየም አለመኖሩ ትልቅ ችግር ሆኖ ቀጥሏል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ እንዲጫወት ማስገደዱንና ፌዴሬሽኑን ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉን ተናግረዋል።
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሚያወጣው ወጪ የበጀት እጥረት እንዲገጥመው ማድረጉና መንግስት ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚፈለገውን ውጤት እያመጣ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ብሔራዊ ቡድኑ የተሻለ ውጤት እንዲያገኝ የጋራ ጥረትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ክለቦች ለክለብ ላይሰንሲንግ አሰራር ተገዢ በመሆንና የሴቶችና የታዳጊ ቡድኖች በማቋቋም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ለታዳጊዎች እግር ኳስ ልማት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጠቅላላ ጉባኤ አባል እንዲሆን የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በጉባዔው ጸድቋል።
ክልሉ የጠቅላላ ጉባኤው አባል የሆነው አዲስ የተቋቋመ ክልል በቀጥታ የጉባኤው አባል ይሆናል በሚለው የአሰራር ደንብ አማካኝነት ነው።
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2016 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
በቀጣይ የ2017 ዓ.ም የእቅድ ሪፖርት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።