ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ሰፊ ጠቀሜታን ይዞ መጥቷል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ):- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው  ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ሰፊ ጠቀሜታን በመፍጠር አስቻይ ሁኔታዎችን ማስገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለፀ።

በሀገሪቱ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ መክፈትና ማስተላለፍ የሚያስችል (unite.et) የተባለ መተግበሪያ በቅርቡ ስራ ላይ ውሏል።

በመተግበሪያው በተፈለገው መጠን የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ መክፈት የሚቻል ሲሆን ተንቀሳቃሽ፣ የቁጠባ እና በጊዜ የተገደበ የውጭ ምንዛሪ በሚሉ አማራጮች ሒሳብ መክፈት እንደሚቻል ነው የተገለፀው ።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው ለኢዜአ እንዳሉት፤  የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዳያስፖራው ማህበረሰብ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይዞ መጥቷል።

ከዚህ ውስጥ የዶላር ምንዛሪ ለውጡ ዳያስፖራው ማህበረሰብ በሕጋዊ መንገድ ገንዘቡን እንዲመነዝርና ሕገ-ወጥነትን እንዲከላከል ማስቻሉን ነው ያነሱት።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ በውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ አካውንት እንዲከፍት መደረጉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፍ እንደሚያስችለው ነው የገለጹት፡፡

ይህም የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚያሳድግ መሆኑን አብራርተዋል ።

ማሻሻያው ዳይስፖራው ማህበረሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገሩ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ  እድል የሚሰጠው እንደሆነም ገልፀዋል።

እንደ አቶ በላይነህ ገለፃ በተያዘው አመት 10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከሪሚታንስ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ዳያስፖራው ማህበረሰብ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ እያጠናከረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥም በቅርቡ በተጀመረው ኢትስ ማይጋርድ በተሰኝ መተግበሪያ በመጠቀም 329 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ዳያስፖራው ማሕበረሰብ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ 50 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በተያዘው ዓመትም  3 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ  ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም