ቀጥታ፡

የቡና ጥራት ደረጃን በማሻሻል  የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው -  ኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ):- የቡና ጥራት ደረጃን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ባለፉት ሦስት ዓመታት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ውጤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ቡናን በክላስተር የማምረት እና ያረጁ የቡና ተክሎችን የመጎንደል ሥራ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት 400 ሺህ ሄክታር የቡና ማሳ የተጎነደለ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ሰዓትም ምርት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት 326 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ አመርቂ ቢሆንም ከጥራት አንጻር ግን መሻሻል የሚገባው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ቡና ጥራት 1ኛ ደረጃ 13 በመቶ ብቻ ሲሆን፤ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የጥራት ደረጃ አራተኛ እና አምስተኛ መሆኑን በአብነት አንስተዋል፡፡

ይህም በዋጋ ደረጃ ሲታይ 50 በመቶ ቅናሽ ስላለው ሀገር ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን ቡና የጥራት ደረጃ ወደ አንደኛ እና ሁለተኛ ከፍ በማድረግ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት፡፡

ይህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ሀገራዊ ገቢን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም አንጻር የቡና አብቃይ አካባቢዎች ከጥራት አንጻር ያሉበትን ደረጃ በመለየት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የይርጋጨፌ፣ ሲዳማ፣ ጉጂ፣ የአርሲ፣ የአሰቦ እና የሊሙ ቡና በአንጻራዊነት የተሻለ የጥራት ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የከፋ፣ የጅማ፣ የኢሊባቦር፣ የበደሌ እና የወለጋ ቡና በብዛት በደረጃ አራት እና አምስት የሚሸጥ በመሆኑ በትኩረት ድጋፍ የማድረግ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የቡና ጥራትን ለማረጋገጥ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑንና በዚህም የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማሳደግ አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም