ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ "ከረሀብ ነጻ የሆነች አለምን መፍጠር ይቻላል" በሚል መሪ ሃሳብ የሚከናወን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ታስተናግዳለች - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከመጪው ጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ "ከረሀብ ነጻ የሆነች አለምን መፍጠር ይቻላል" በሚል መሪ ሃሳብ  የሚከናወን ዓለም አቀፍ ጉባኤን እንደምታስተናግድ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡ 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንደምታስተናግድ ገልጸዋል፡፡

ጉባኤው "ከረሀብ ነጻ የሆነች አለምን መፍጠር ይቻላል" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ጉባዔው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ኢንቨስትመንት ለማጠናከር እና ያለውን መደጋገፍ ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም የረሀብ ችግርን ለመፍታት የኢንቨስትመንትን አስፈላጊነትና የአለም አቀፍ ትብብር ጉዳይን ማሳደግ የጉባኤው አላማዎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

በጉባኤው በዘርፉ እውቀትና ልምድ ያላቸው ተቋማትና ድርጅቶች የሚሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

ጉባኤው የኢትዮጵያ መንግስት፣የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በጋራ እንዳዘጋጁት  ጠቁመዋል።

ለዚህ የሚሆን አቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን ገልጸው ለጉባኤው የሚያስፈልጉ ስራዎች ከ 90 በመቶ በላይ መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ጉባኤው በአለም ላይ እያጋጠሙ ላሉ ተግዳሮቶች የመፍትሄ ሃሳብ የሚመላከትበት መሆኑን አንስተዋል።

ዛሬ ያለችው አለም ሳይንስና ቴክኖሎጂ የቀየራት መሆኑን ገልጸው በጉባኤው ዘላቂ መፍትሄን ለማምጣት በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ጉባኤው እንደ አገር አዳዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንዲሁም የንግድ ግንኙነቶችን ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸው ይህም ቀጣይነት ያለው የመተባበር እና የመደጋገፍ ሁኔታን የሚያጠናክር መሆኑን አመላክተዋል።

ባለፉት ስድስት አመታት ኢትዮጵያ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፍ በርካታ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን ማስመዝገቧን ገልጸው በመድረኩ የተገኙ ውጤቶች በተሞክሮ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።

ገቢ ምርትን ለመተካት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ስራዎች በጉባዔው ላይ እንደሚቀርቡና በዚህም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም