የኢትዮጵያ ታዳጊዎች በዓለም አቀፍ የስፔስ ኦሊምፒያድ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አገኙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታዳጊዎች በዓለም አቀፍ የስፔስ ኦሊምፒያድ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አገኙ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በመጀመሪያ የዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚ ኦሎምፒያድ ተሳትፏቸው የብር እና ነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ ማስመዝገባቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሩሲያ ሶቺ ክልል ሲሪየስ ከተማ በተከናወነው ዓለም አቀፍ አስትሮኖሚ ኦሎምፒያድ (OWAO2024) ኢትዮጵያን ጨምሮ 20 ሀገራት ተካፍለዋል።
እያንዳንዳቸው እድሜያቸው 18 እና ከዚያ በታች የሆኑ ቁጥራቸው ከ4 እስከ 6 የሚደርሱ በመስኩ ልዩ ተሰጥኦ እና ዝንባሌ ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች በውድድሩ ላይ ተሳትፈዋል።
ይህ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ተሳትፎ ነው፡፡
በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስትቲዩት ስር በተደራጀው የኢትዮጵያ ልጆች የስፔስ ክህሎት ማሳደጊያ ማዕከል ላለፉት አራት አመታት በክረምት ወራት ስልጠና ሲወስዱ የቆዩ 5 ታዳጊ ወጣቶች በውድድሩ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ተማሪ ፍትሕ ግርማ የብር ሜዳሊያ፣ ተማሪ ሚካዔል አሸናፊ እና ተማሪ አላዛር አዳነ እያንዳንዳቸው የነሐስ ሜዳሊያ፣ ተማሪ ሙሳ ከድር የብርቱ ተወዳዳሪ የክብር ሽልማት አግኝተዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ እና የታዳጊ ወጣቶቹ ቡድን አስተባባሪ ኢንጂነር ግዮን አሸናፊ ከፈተናው ክብደት እና ከተወዳዳሪዎቹ ጥንካሬ አንጻር ታዳጊዎቻችን ያሳዩት የውድድር ብቃት የሚደነቅ ሲሆን፤ በቀጣይ የስልጠና አካሄዳችን በይበልጥ ለማሻሻል ምን ላይ ማተኮር እንዳለብን የተማርንበት ነው ብለዋል፡፡
በኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በውድድሩ የተሳተፉ ታዳጊ ተማሪዎቻችንን እና ወላጆቻቸውን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ፤ ሌሎች ታዳጊዎችም አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ጥሪ ማቅረቡን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።