በ2016 በጀት አመት የተሻለ የታክስ ተገዥነት ላስመዘገቡ 550 ታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2017(ኢዜአ)፦ በ2016 በጀት አመት የተሻለ የታክስ ተገዥነት ላስመዘገቡ 550 ታማኝ ግብር ከፋዮች መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም እውቅና ይሰጣል።

የዕውቅና መርሃ ግብሩን አስመልከቶ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እና የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በጋራ መግለጫ ስጥተዋል።

ዕውቅናው በ2016 በጀት አመት በህግ ተገዥነትና ግብርን በወቅቱ በመክፈል የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አካላት የሚሰጥ መሆኑን ኃላፊዎቹ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ የአገር ምጣኔ ሀብት ከሚያመነጨው አንጻር የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻልና አሰራርን በማዘመን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከአመት ወደ አመት የሚሰበሰበው የገቢ መጠን እያደገ መምጣቱን ገልጸው በ 2016 በጀት አመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 529 ቢሊዮን ብር ውስጥ 512 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ግብር ከፋዮች ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በማሳወቅና በመክፈል ያሳዩት ሚና ለገቢው ማደግ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አንስተዋል።

በመሆኑም በፌዴራል ደረጃ የታክስ ህግን በማክበርና በወቅቱ ግብርን በመክፈል የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 550 ግብር ከፋዮች መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የዕውቅናው አላማ ለአገራቸው ግብርን በታማኝነት የሚከፍሉትን በማበረታታት ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ ለማድረግ መሆን ጠቅሰዋል፡፡

የሚሰጠው ዕውቅና የወርቅ፣ ፕላቲኒየምና የብር በሚል ሶስት ደረጃዎች እንዳሉትም አስታውቀዋል።

ዕውቅናው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን ተከትሎ የሚሰበሰበውን ገቢ በማሳደግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚረዳ ንቅናቄ ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል ሚኒስትሯ።


 

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ዕውቅናው ለሌሎች ተነሳሽነትን በመፍጠር የህግ ተገዥነትና ታማኝነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የዚህ አመት የታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና ለ6ኛ ጊዜ የሚሰጥ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም