ቀጥታ፡

ማሰልጠኛ ማዕከሉ ብቃት ያለው ወታደር ለማውጣት እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት -ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ

ሀዋሳ ፤መስከረም 27/2017(ኢዜአ)፦ የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚችል ብቃት ያለው ወታደር ለማውጣት እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ አስታወቁ።

የተኩስ አመራር ሃላፊና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ ከፍተኛ ወታደራዊ አማካሪ ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከልን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት እንዳሉት፣ የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅና በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጸ ብቁ ሠራዊት በማፍራት ረገድ ትልቅ አስተዋጾ እያደረገ ነው።

ማሰልጠኛ ማዕከሉ የሚያሰለጥናቸውን ወታደሮች በአካል ብቃት፣ በስልትና በወታደራዊ ትምህርት በማነጽ ለሀገር ክብር የቆሙ በርካታ ጀግኖችን ማፍራት እንደቻለ ገልጸዋል።


 

ከአካል ብቃት አንስቶ እስከ ስልት ወረዳ ያለውን የስልጠና ሂደት ተዘዋውረው እንደጎበኙ የተናገሩት ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት፤ በጉብኝቱም ሰልጣኞቹ ጥሩ ስልጠና እንደወሰዱ መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ከአካል ብቃት አንስቶ እስከ ስልት ድረስ ለሚሰጣቸው ስልጠናዎች ምቹ የማሰልጠኛ ስፍራዎችን በማዘጋጀት ሰልጣኞቹ ብቁ ወታደር ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

"ታሪካዊ ጠላቶቻችን አስተባባሪነት የውስጥ ታጣቂ ሽፍቶችን በመጠቀም ሀገራችንን ለማተራመስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደማይሳካላቸው የሠራዊታቸው አቋም አመላካች ነው" ብለዋል።

የውጭ ሀይሎች ፍላጎት በፍጹም የሚሳካ እንዳልሆነ የገለጹት ሌተናል ጄነራሉ፣ "በማሰልጠኛው ያየነው ስልጠናና የሰልጣኞች አቅም የጥፋት ሀይሎች ተልዕኮ እንደማይሳካ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።

በብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ስልጠና ከወሰዱ ውስጥ መሰረታዊ ወታደር ነጻነት ታከለ እንዳለችው በማዕከሉ ላለፉት አራት ወራት ስልጠና መውሰዷን ተናግራለች።


 

“ይህም በስነ ልቡናና በአካል ብቃት እንድጎለበት አድርጎኛል፤ አሁን ብቁ በመሆኔ ለሚሰጠኝም ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ብላለች።

ሌላው አስተያየት ሰጪ መሰረታዊ ወታደር ዮናስ ሞሲሳ ማሰልጠኛ ከገባሁ በኋላ ሥነልቦናዬንና አካል ብቃቴን የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን ወስጂያለሁ ብሏል።


 

የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል ትናንት ሁለተኛ ዙር መሰረታዊ ወታደሮችን አስልጥኖ ማስመረቁ የሚታወስ ነው።

ማዕከሉ የኮማንዶ፣ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ፣ የልዩ ሃይል ጸረ ሽብር ማሰልጠኛና የአመራር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶችን በማደራጀት የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ የሚገኝ ማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑም ተገልጿል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም