የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ይገኛል-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ይገኛል-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ይገኛል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ እየተሸጋገረች መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የዜጎችን የተጠቃሚነት ደረጃ በደረጃ እያሳደገ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም የ8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንም አንስተዋል።
የግብርና ዘርፉ ብቻ በ6 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በዋና ዋና ሰብሎች 700 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
በመኸርና በመስኖ ልማትም 230 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰው፤የስንዴ ምርትን ለወጪ ገበያ የማቅረቡ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
በሌማት ትሩፋትና የፍራፍሬ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችም የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ የተሻለ ስራ እንዲከናወን ማስቻላቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ከሸቀጦች ወጪ ንግድ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱንና 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ያወጡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚው እየተነቃቃ ከመሄዱ ጋር ተያይዞም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 379 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ነው የተናገሩት፡፡