ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ እንዲሆንና የጋራ ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት ትሰራለች-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ እንዲሆንና የጋራ ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት ትሰራለች-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ እንዲሆንና የጋራ ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደምትሰራ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሰይመዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ እንዲሆን ኢትዮጵያ ብርቱ ጥረት ማድረጓን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ በጋራ መልማት እንዲሁም በቀጣናዊ ትስስር ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሰጥቶ መቀበል መርህ አማራጭ ወደብና የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ትኩሳት ለማርገብ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተደማጭነት በማስፋት በቀጣናው ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በሱዳን የተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት አግኝቶ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ኢጋድና የአፍሪካ ህብረት ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ኢትዮጵያም ግልጽና ተከታታይ የሰላም ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሁለትዮሽ ግንኙነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተው፤ ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት በወቅቶች የማይለዋወጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል፡፡
ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅም ካላቸው የባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ መደበኛና ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሸጋገር ነባር ስትራቴጂያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከርና አዳዲስ ግኑኝነት መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ ተደማጭነትና ተጽፅኖ ፈጣሪነት እንዲጎለብት መደረጉን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል እንድትሆን የተከናወኑ ተግባራትንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
በቀጣይም የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ እንዲሆንና የጋራ ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ወዳጆች የማብዛት ሥራም በስፋት እንደሚከናወን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።