ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ አማራጭ የወደብ እና የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ

አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ አማራጭ የወደብ እና የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያን ወዳጆች እና አጋሮች የማበርከትና የማብዛት ስራም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ተካሄዷል።

ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ለሁለቱ የፌዴራል መንግሥት ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን መጀመራቸውን በማብሰር የፌዴራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ አቅርበዋል።

በዲፕሎማሲው ረገድ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን ሁለንተናዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር አገራዊ ጥቅሞችን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላምና በጸጥታ ጉዳይ በኢኮኖሚ ጉዳዮች በቀጣናዊ ትስስር የጋራ ጥቅም የሚያስገኙ ስራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸውም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ሰጥቶ በመቀበል መርህ አማራጭ የወደብ እና የባህር በር እንድታገኝ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተጀመረው ጥረት መሰረት ያደረገ የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያላንድ ጋር መፈረሙን ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን አላስፈላጊ የዲፕሎማሲ ትኩሳት ለማርገብ እና የአገርን ስም ለማጠልሸት የሚካሄደውን ዘመቻ ለመከላከል በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ በቀጣናው በጋራ የመልማት እና በጋራ የማደግ ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተደማጭነት በማስፋት ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉልህ ስራዎች መከናወናቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን በተለይም የሱዳን ግጭት እንዲፈታ ኢትዮጵያ የጀመረችው ግልጽና ተከታታይነት ያለው የሰላም ዲፕሎማሲ ስራ እንደሚቀጥልም ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደህንት እንዲረጋገጥ ጉልህ ተሳትፎ እንደምታደርግም ጠቅሰዋል።

በሁለትዮሽ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሞችን በማስጠበቅ ከቻይና ጋር ያለንን ግንኙነት በወቅቶች የማይለውጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ እንዲል መደረጉን አንስተዋል።

ፓለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ካላቸው የባህረ ሰላጤው አገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗ ሚዛናዊ ግንኙነት እንዲኖራትና ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን ለማግኘት እንደሚያስችላትም አንስተዋል።

በባለ ብዝሃ ወገን የዲፕሎማሲ መድረክ የኢትዮጵያ ተደማጭነት እና በጎ ተጽእኖ ፈጣሪነት የሚያሳድጉ ጉልህ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር እና አዳዲስ ስትራቴጂካዊ አጋሮችን የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ትሰራለች ብለዋል።

የኢትዮጵያን ወዳጆች እና አጋሮች የማበርከትና የማብዛት ስራ በትኩረት እንደሚሰራበትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም