ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ከሚያመላክቱ ሥራዎች ዋነኛው ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ከሚያመላክቱ ሥራዎች ዋነኛው ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤መስከረም 27/2017 (ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ከሚያመላክቱ ሥራዎች ዋነኛው ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶችም መክፈቻ መድረክ ላይ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አድርገው ሰይመዋል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ከሚያመላክቱ ትላልቅ ሥራዎች ዋነኛው ነው ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕዳሴው ግድብ አምስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተካሂዷል፤ የግድቡ የሲቪል ምህንድስና ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል ሲሉም ተናግረዋል።
ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጀ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋጽዖ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ተጽፎ የሚቀመጥ አበርክቶ አድርጓል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የሕዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ማመንጫ ብቻ ተብሎ የሚወሰድ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዘመናት ህልም ወደሚጨበጥ ስኬት የተቀየረበት ነው ብለዋል፡፡
የሕዳሴው ግድብ ስኬት ኢትዮጵያ የራሷን የዕድገት ትልም በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል ለዓለምያሳየችበት ነው ሲሉም አክለዋል።
ግድቡ የጎረቤት አገሮችን የመልማት ፍላጎት ይደግፋል፤ የተፋሰስ አገራትን ስጋት እንደሚቀንስም ነው ፕሬዝዳንቱ አያይዘው የገለጹት።
በአጠቃላይ ዓመቱ የኢትዮጵያ አሸናፊነት የታየበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።