በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚዎች ሆነዋል-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚዎች ሆነዋል-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2017(ኢዜአ) ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚዎች ሆነዋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ተናገሩ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶችም አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት አድርገው ሰይመዋል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፤ መንግስት በሰው ተኮር ተግባራት አማካኝነት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ረገድ በተለይ አምራችና ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት ጉልህ ሚና እያበረከተ ያለውን የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሆናዋል ነው ያሉት፡፡
በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር አማካኝነትም ከ15 ሺህ 500 በላይ ትምህርት ቤቶችን መጠገንና ከ5 ሺህ 900 በላይ ተጨማሪ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ሽፋን 89 ነጥብ 4 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አውስተዋል፡፡
በሌላ በኩል ማዕድ በማጋራትና የአቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤት በማደስ በማህበራዊ ዘርፍ የኢትዮጵያ እድገት አካታች እንዲሆን በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ነው ያነሱት፡፡