ቀጥታ፡

አቶ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያ ሴናተር ኒኮላይ ቪላዲሚሮቭ ከተመራ የልዑክ ቡድን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2017(ኢዜአ)፡- የፌዴሬሸን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያ ሴናተር ኒኮላይ ቪላዲሚሮቭ ከተመራው የልዑክ ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

አቶ አገኘሁ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የረጅም ዘመን የታሪክና የባህል ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውና ስምምነቱ ፈጥኖ ወደ ተግባር እንዲገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

ምክር ቤቱ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አስተዳደር  ዙሪያ ከሩሲያ ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአቅም ግንባታ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሩሲያን ድጋፍ እንደማይለያት የጠቀሱት አቶ አገኘሁ በብሪክስ አባል ሀገራት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ተግታ እንደምትሰራም ነው የገለጹት።

የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ ምኞት እንደሆነም ተናግረዋል።


 

የሩሲያው ሴናተር ኒኮላይ ቪላዲሚሮቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሩሲያ ጠንካራ ወዳጅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

ሩሲያ በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባህል ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አመልክተዋል።

የሩሲያን ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ የመክፈት ፍላጎት እንዳለም አንስተዋል።

ሩሲያ የብሪክስ አባል ሀገራት ሰብሳቢ በመሆኗ አባላቱ በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና የጽህፈት ቤቱ የማኔጅመንት ቡድን መገኘቱን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም