ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ዛሬ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ዛሬ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 27/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ዩጋንዳ ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ አገራት ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ይደረጋል።
24ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ትናንት በታንዛንያ ተጀምሯል።
በማጣሪያ ውድድሩ ላይ ዘጠኝ አገራት ተሳታፊ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ በማጣሪያው በምድብ 2 ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።
በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያከናውናል።
20 ተጫዋቾችን የያዘው ስብስብ ቅዳሜ አርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዳሬሰላም መግባቱ ይታወቃል።
ተጫዋቾቹ ላለፉት ሁለት ቀናት በታንዛንያ ልምምዳቸውን አድርገዋል።
ቡድኑ ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በኪኖንዶኒ ሙኒሲፓል ካውንስል ስታዲየም ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በ46 ዓመቱ ማቲያስ ሉሌ የሚመራው የዩጋንዳ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 20 ተጫዋቾችን ይዞ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
በምድብ 2 ሌላኛው መርሃ ግብር ደቡብ ሱዳን ከብሩንዲ ከቀኑ 10 ሰዓት በኪኖንዶኒ ሙኒሲፓል ካውንስል ስታዲየም ይጫወታሉ።
በማጣሪያው በምድብ አንድ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ በምድብ አንድ ተደልድለዋል።
በዚሁ ምድብ ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ሱዳን ጅቡቲን 3 ለ 1 እንዲሁም ኬንያ ታንዛያን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።
የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።