ቀጥታ፡

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ኃይል ወደማመንጨት መሸጋገሩ የኩራት ምንጭ ሆኗል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2017(ኢዜአ):- የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ኃይል ወደማመንጨት መሸጋገሩ የድጋፍ ውጤታችንን ከማየት በዘለለ የኩራት ምንጭ ሆኖናል ሲሉ የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሠሠና የማኅበሩ የቦርድ አባል ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሕዳሴ ግድብ በትብብር እውን የሆነ የኢትዮጵዊያን ዳግማዊ የዓድዋ ድል መገለጫ ነው።

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ፤ በአሜሪካ ችካጎ ግዛት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ሁለት ጊዜ ቦንድ ገዝቼ አሻራየን አሳርፊያለሁ ብሏል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጥቁር አፍሪካዊያን በራሳቸው አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚችሉ ምሳሌ የሆነ የኢትዮጵያዊያን ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን ገልጿል።

ግድቡ ኃይል ወደማመንጨት መሸጋገሩም በውጭ አገራት በሚኖራቸው የሥራ እንቅስቃሴ ከሌሎች ዓለማት ዜጎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ብሔራዊ የኩራት ምንጭ እንደሆናቸው ተናግሯል። 


 

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር የቦርድ አባል ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፤ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጅማሮ ማግስት ወደጉባ በማቅናት በአውሮፕላን አብራሪነት አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ግዙፍ የኃይል አማራጭ ፕሮጀክት ብርሃን ወደመስጠት መሸጋገሩም በህይወት አጋጣሚዬ ካየኋቸው ትላልቅ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያን ትንሳኤ የማይበት መስታወት ነው ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ ስኬትም የኃይል አቅርቦት ፍላጎት በማሟላት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል  ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ቀጣናዊ የፖለቲካና የኃይል አቅም በማጠናከር ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ሰላምና የኃይል ትስስር የማይተካ ሚና ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነም ገልጸዋል።

ለቀጣናው አገራትም በሚፈጥረው የኃይል ትስስር አማካኝነት በትብብር ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማሳለጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በግድቡ ግንባታ ላይ የሚያነሱት ወቀሳም ከውኃ አቅርቦት ጋር የሚያያዝ ሳይሆን የተፈጥሮ ኃብቷን ተጠቅማ ዕድገቷን እንዳታሳልጥ ከማሰብ የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።

መሰል የልማት ፕሮጀክቶች መገንባታቸው የኢትዮጵያን ከፍታ ማስቆም የሚችል ኃይል እንደሌለ ማሳያ እንደሆነም አንስተዋል።

በቀጣይም ማኅበሩ በማጠናቀቂያ የግንባታ ምዕራፍ ላይ ለሚገኘው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን በማስተባበር የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያን ትብብር አጠቃላይ የግንባታ አፈፃጸም 95 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከጀመረም ሰነባብቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም